Thursday, May 8, 2008

To Whom Does Gonder Belong To?


ጎንደር የየትኛዉ ዘር ድርሻ ብትሆን ነዉ
አንዱን “ባለ ዘር” ሌላዉን “ዘረቢስ” የሚባለዉ?


ከአያያዝ ይቀደዳል ካነጋገር ይፈረዳል ይላሉ ቀደምት።ሰዎች ሃሳባቸዉን ለመግለጽ ቃላት ይጠቀማሉ። ሃሳብ ሰፊ ራዕይ ነዉና በቃላት ይገለጻል። ዳርቻም የለዉ።ቃል ለበጎም ለክፉም አገላለጽ እንደሚጠቅሙን እናቃለን።አንደ በጎ እና አንደ ክፉ ሰዉ ሁሉ በጎም ክፉም ቃላቶች አሉ። በጎ ቃል የሰዉን ሞራል ከፍ አድርጎ ወንድማዊነትን ሰባዊነትን ያዳብራል።ክፉ ቃል ግን ህሊናን ይደቁሳል። ያዉም ከክፉም ክፉ ቃል “አጥንት ሰባሪ” የሚሉት አበዉ።

ደራሲ ከበደ ሚካኤል “ስልጣኔ ማለት ምን ምንድነች” በሚል መጽሃፋቸዉ ላይ አንደገለጹት፤በቃል ምክንያት በመካከላቸዉ አለመግባበት እየተፈጠረ ሰዎችና መንግሰታት ብዙ ደም ፈሷል።….ሊቃዉንት ያለማቋረጥ ሲነጋገሩ ከርመዉ በመጨረሻ ሳይስማሙ ሁሉም ቅር ብሏቸዉ ይለያያሉ። ምክንያቱም የማያስማሙ ቃሎች በመኖራቸዉ ነዉ።>>

ከትናንት በስትያ ዓይጋ ፎረም እየተባለ በሚጠራዉ ድረገጽ ስለጎንደርና ስለዘር አነስቶ የሚያትት የሚመስል ቁጣ የተሞላበት ዘረኛ ስድብ ለጥፎ ነበር። ድረ ገጹ ላይ የሚጻፉ ጽሁፎች መለስ ዜናዉን ሲያሞግሱና ሲያወድሱ በላያቸዉ ላይ ፀሃይ ስለምትጠለቅባቸዉ መስጠዉኝ የማነብባቸዉ ጊዜያት እምብዛም ነዉ። በድረ ገጹ ላይ በጎንደር፤ በጎጃምና በሱዳን ዳርቻዎች የሞኖሩ ገበሬዎች ለአመታት የቆዩ አለምግባባቶች እነደነበሩና አሁንም አንዳሉ አይታበልም። ከኢትዮጵያ ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህነን አስመልክተዉ ያስሰሙት አቤቱታና ቅሬታ፤ የወያኔዎቹ አፈቀላጤዎች በድረገጻቸዉ የሰጡት ምላሽ << ጎንደር ኤይንት ዩር ማማ ኤኒሞር>>፤ ከሚለዉ አንዳንድ አሜሪካኖች “የእሪ በከንቱ” ሰፈርተኞች ቋንቋ ከሚሉትአንስቶ አስከ <<ዘረቢሶች>> የሚለዉ የፋስስቶችና የጉልተኞች የስድብ ቋነቋ በዚህ ክፍለዘመን በመጠቀማቸዉ የተገረማችሁ ልትኖሩ ትችሉ ይሆናል። ቢሆንም፤ ወያኔዎችና አገልጋዮቻቸዉ ስለ ኢትዮጵያና ስለሰነደቃላማዋ ትክሻዋ ከሚሸከመዉ በላይ ዘለፋዉ ከመለስ ዜናዊ ጀምሮ አስከ ዳዊት ዮሐንስ፤ተፈራ ዋልዋ፤ታምራት ላይኔ…አስከ……አስከ….አስከ….ድረስ ያሉት ሰዎች ያልተባለ የለም። ሰዎቹ የሚፈሩት የላቸዉም።ለፈጣሪም ለአገርም።

የዘረኞቹ አፍ’ላፊ ዘለፋቸዉ ዛሬም በተቃዋሚነት የቆሙትን የቤጌምድር/ጎንደር ተወላጆችና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ አንጉደዉታል።እንደሚታወቀዉ በጎጃምና በጎንደር አካባቢ አንደዚሁም በሌሎች ቦታዎች በተለያዩ ጊዜያት በሱዳን በኩል ባካባቢዉ ገበሬዎች ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩት ጥቃቶች በድምጽ ማጉያ የተቀዱ የገበሬዎቹ ቃለማጠይቆችና እሮሮዎች ባንዳንዶቻችን አጅ ዛሬም ይገኛሉ (ካልተሳሳትኩ በነፃነት ለኢትዮጵያ ራዲዮ በድሮ አርካኢቩ ዉስጥ አይታጣም)።በቃለመጠይቁና በተደመጠዉ የገበሬዎቹ እሮሮ ፤<መንግስት በሉኝ!> የወያኔዉ ቡድን እንዳልደረሰላቸዉና አንዳልተከላከለላቸዉ ሪከርዱ/መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ይህ እየታወቀ፤ በማስረጃ ከመመከት ይልቅ ለገበሬዉ ህለዉናና ለዜጎቹ የቆመን ኢትዮጵያዊያን ከጎንደርም ይወለድ ከጎንደር ዉጭ፤<ዘረቢስ> ተብሎ ዘረኝነትን የሚያጎላ ስድብ የሚዘለፍበት ምንም ዓይነት ምክንያት አልነበረም።
በመሰረቱ


<ዘር> በጉዳዩ ላይ ለምን ማንሳት አንደተፈለገ ባይገባንም፤ ወያኔዎችና የወያኔዉ የአማርኛ ክፍል ተብሎ የሚታወቀዉ የበረከት ስምኦኑ “ብአዲን” ጫካ ለቀዉ ወደ መንግስትነት ከገቡ ከ1991 ጀምሮ የሰነዘሩዋቸዉ የዘረኝነት ቃላቶች ቢለቀሙ ዳጎስ ያለ መጽሀፍ ይወጣበት አንደነበር እርገጠኛ ነኝ። አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዜጎቹ ስለቆመ “ዘርህ የት ነዉ? ዘርህ አይታወቅም፤ የማን ዘር ነህ? ዘረቢስ ነህ! ዘረቢሶች ናቸዉ! የማሳሰሉ በደምና በአጥንት በዘመድ አዝማድ በላሸቀ የዘር ቆጠራ ያደገ የጉልተኛ አና የፋሽስቶች ህሊና ባለንበት ዘመንና በተጓዝንባቸዉ የዘመናት ርቀቶች በዘመናችነ መጥፋት ነበረበት። ሆኖም በወያኔና ተከታዮቹ የተለመደ በመሆኑ ከዚያ አስጸያፊ የዘር ስድብ ልማድ መላቀቅ አልቻሉም።

በመሰረቱ አንኳንና ኢትዮጵያዊ ሰዉ፤ አትክለቶችና አዝርዕት ዘር አላቸዉ። የአንድ ቤተስብ ግንድ ናቸዉ። ዘረቢስ የሚባል ዘር የሌለዉ ነገር በዚህ አለም ዉስጥ የለም። ዘር የለህም፤ ዘረቢስ ነህ፤ አናዉቅህም፤የኛ ዘር የለብህም፤ ባዕድ ነህ፤ አገርህም ሰማይህም አይታወቅ…..ወዘተ እያሉ የዜጋነት ከልካይና ፈቃጅ ሆነዉ ራሳቸዉ ያስቀመጡ የዘመናችን ግልገል ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ምድር መብቀላቸዉ ያሳዝናል።
ችግሩ በስፋት ከየዓለማቱ በጥራጊ መልክ ወደ ኢትዮጵያ የመጣዉ አፓርታይድና ፋሽዝም ይፋ ሆኖ ለጎብዎች የሚነበብ ነጋሪት (ማስታወቂያ) አልወጣም አንጂ፤ ቢወጣ ኖሮ የጦቢያዉ ጸሃፊ አቶ ጸጋየ ገ/መድህን አርአያ ያስቀመጡትን ዓይነት ማስታወቂያ በምድሪቱ ለይ መለጠፍ ነበረበት። ልጥቀስና በዛዉ ልሰናበት፦

<< የሰላምሐዋርያት ወደ ሚኮነኑባት ዓለም አንኻን ደህና መጡ! ነቢያት ዛሬም ወደ ሚወገሩበት መዲና ጥሩ እግር ጥለዎታል። ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የወጣዉ አፓርታይድና ፋሺዝም ሥር እየሰደዱ በሚገኙበት አሮጌ አገር አዳዲስ ጋንግስተሮችን ያገኛሉ። ማስታወሻ ደብተርዎን ይቆጥቡ።ብዙ የሚያስጽፍ ድርጊት አለና! ለማንኛዉም እንኳን ወደማፊያዎች አገር መጣ! ስለሕግና ስለሕጋዊነት ብዙ ይሰማሉ! እንኳን ደህና መጡ ብቻ!>…..< ስለንግድና እንቅስቃሴ የሚአስተምረዉን ሥነ ኣእምሮ አወቃለሁ ባልልም ቱሪስት ድርጅት (እሱም ስሙን ቀይሮ ካልሆነ) የተነሳሁበትን ዓይነት ማስታወቂያ ገና ከቦሌ እላይ እና ቀጥሎም የአራዳነት ማእከል በሆነዉ ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወረድ ብሎ ቢለጠፍ ከ24ቱ የዓለም ድንቅ ነገሮች አንደኛዉ አንደሚሆን እገምታለሁ።>> (ጸጋየ ገ/መድህን አርአያ ጦቢያ ቁጥር 10/1993)

አዎን ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የመጣዉ አፓርታይድና ፋሺዝም አንደ ዱባ ሥር እሰደደደ የሚገኝባት አሮጌ አገር፤ ባለ ዘሮቹ <ዘረቢሶች> ናችሁ ቢሉን ከስርዓቱ ባሕሪይ የተያያዘ በመሆኑ ለመነጋገርያ እና ሌሎች ማስገነዘቢያ ይረባ አንደሆን አንጂ ሰዎቹ ቢወቀሱም ቢመከሩም “ተፈጥሮን ተመክሮ” ሊያድነዉና ሊመልሰዉ እነደማይችል ከነ በኒቶ እና ከነ ሂትለር ወል ባሕረይ ተገንዝበናል።

ኢትዮጵያ በነጻነትዋ ለዘላለም ትኑር!
ጌታቸዉ ረዳ